ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 21:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የበደልሁት እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ።

18. ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።

19. ዳዊትም ጋድ በእግዚአብሔር ስም በነገረው ቃል መሠረት ለመፈጸም ወጣ።

20. ኦርና ስንዴ በመውቃት ላይ ሳለ ዘወር ሲል መልአኩን አየ፤ አብረውት የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ።

21. ዳዊት ወደ እርሱ እየቀረበ መጣ፤ ኦርና ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ዳዊትን አየው፤ ከዐውድማውም ወጥቶ መሬት ላይ ለጥ ብሎ በመደፋት ለዳዊት እጅ ነሣ።

22. ዳዊትም፣ “በሕዝቡ ላይ የወረደው መቅሠፍት እንዲወገድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ዐውድማህን ልውሰደው፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው።

23. ኦርናም ዳዊትን፣ “እንዲሁ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሥ ደስ ያለውን ያድርግ፤ እነሆ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎቹን፣ መውቂያ በትሮቹን ለማቀጣጠያ ዕንጨት፣ ስንዴውን ደግሞ ለእህል ቍርባን እንዲሆን እሰጣለሁ፤ ሁሉንም እኔ እሰጣለሁ።” አለ።

24. ንጉሥ ዳዊት ግን ለኦርና “አይደረግም፤ ሙሉውን ዋጋ እኔ እከፍላለሁ፤ የአንተ የሆነውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ አልፈልግም፤ ዋጋ ያልከፈልሁበትንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” ሲል መለሰለት።

25. ስለዚህ ዳዊት ለኦርና የቦታውን ዋጋ ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ ከፈለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 21