ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 16:31-41 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድር ሐሤት ታድርግ፤በአሕዛብም መካከል፤ “እግዚአብሔር ነገሠ!” ይበሉ።

32. ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ይናወጥ፤ሜዳዎችና በእርሷ ላይ ያሉ ሁሉ ሐሤት ያድርጉ።

33. ያን ጊዜ የዱር ዛፎች በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤በደስታ ይዘምራሉ፤በምድረ በዳ ላይ ሊፈርድ ይመጣልና።

34. ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

35. “አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ ታደገን፤ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤ከአሕዛብም መካከል ታደገን”ብላችሁ ጩኹ።

36. ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “አሜን፤ እግዚአብሔር ይመስገን” አሉ።

37. ዳዊትም ለእያንዳንዱ ቀን በተመደበው መሠረት ዘወትር እንዲያገለግሉ አሳፍንና የሥራ ባልደረቦቹን በዚያው በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው።

38. እንዲሁም ዖቤድኤዶምና ሥልሳ ስምንቱ የሥራ ባልደረቦቹ አብረዋቸው እንዲያገለግሉ በዚያው ተዋቸው። የኤዶታም ልጅ ዖቤድኤዶምና ሖሳ የቅጥሩ በር ጠባቂዎች ሆኑ።

39. ዳዊት ካህኑን ሳዶቅንና የሥራ ባልደረቦቹን ካህናት በገባዖን ከፍተኛ ቦታ ላይ በሚገኘው በእግዚአብሔር ድንኳን ተዋቸው፤

40. የተዋቸውም ለእስራኤል በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት በእግዚእብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ጧትና ማታ በየጊዜው እንዲያቀርቡ ነው።

41. እንዲሁም “ፍቅሩ ለዘላለም ነውና” እያሉ እንዲያቀርቡ ኤማንና ኤዶታም እንዲሁም ተመርጠውና ስማቸው ተመዝግቦ የተመደቡ ሌሎችም አብረዋቸው ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 16