ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ።

2. ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ።

3. ከዚያም ለእስራኤል ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ጥፍጥፍ ተምር፣ ሙዳ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ ጥፍጥፍ ዘቢብ ሰጠ።

4. በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እንዲያገለግሉና ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ልመና፣ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርቡ ከሌዋውያን ሰዎች ሾመ፤

5. አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱ ቀጥሎ ዘካርያስ ሁለተኛ ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያም ይዒኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ መቲትያ፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ ዖቤድኤዶም፣ ይዒኤል ተሾሙ፤ እነርሱም በመሰንቆና በበገና ይዘምሩ ነበር፤ አሳፍ ደግሞ ጸናጽል የሚጸነጽል ሆኖ ተመደበ።

6. እንዲሁም ካህናቱ በናያስና የሕዚኤል ዘወትር በእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ፊት መለከት እንዲነፉ ተመደቡ።

የዳዊት የምስጋና መዝሙር

7. በዚያም ቀን ዳዊት በመጀመሪያ ለአሳፍና ለሥራ ጓደኞቹ ይህን የእግዚአብሔር ምስጋና መዝሙር ሰጠ፤

8. ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ፤ ስሙንም ጥሩ፤ለአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ንገሩ፤

9. ዘምሩለት፤ ውዳሴም አቅርቡለት፤ድንቅ ሥራውን ሁሉ ንገሩ፤

10. በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ።

11. ወደ እግዚአብሔርና ወደ ኀይሉ ተመልከቱ፤ዘወትር ፊቱን ፈልጉ።

12. ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤

13. እናንተ የባሪያው የእስራኤል ዘሮች፣እናንተ የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች።

14. እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው፤

15. ኪዳኑን እስከ ዘላለም፣ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺህ ትውልድ ያስባል።

16. ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን፣ለይስሐቅ የማለውን መሐላ።

17. ይህንንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ አጸና፤ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አደረገ፤

18. እንዲህ ሲል፣ “የምትወርሰው ርስት እንዲሆን፣የከነዓንን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ።”

19. ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣በእርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣

20. ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው መንግሥት ተንከራተቱ።

21. ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤

22. እንዲህ ሲል፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤በነቢያቴ ላይ ክፉ አታድርጉ።

23. ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ።

24. ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ።

25. እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምስጋናውም ብዙ ነው፤ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ የሚገባው ነው።

26. የአሕዛብ ሁሉ አማልክት ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።

27. በፊቱ ክብርና ሞገስ አለ፤ብርታትና ደስታም በማደሪያው ስፍራ።

28. የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር ስጡ፤ክብርና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።

29. ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ስገዱ።

30. ምድር ሁሉ በፊቱ ትንቀጥቀጥ፤ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥምም።

31. ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድር ሐሤት ታድርግ፤በአሕዛብም መካከል፤ “እግዚአብሔር ነገሠ!” ይበሉ።

32. ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ይናወጥ፤ሜዳዎችና በእርሷ ላይ ያሉ ሁሉ ሐሤት ያድርጉ።

33. ያን ጊዜ የዱር ዛፎች በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤በደስታ ይዘምራሉ፤በምድረ በዳ ላይ ሊፈርድ ይመጣልና።

34. ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

35. “አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ ታደገን፤ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤ከአሕዛብም መካከል ታደገን”ብላችሁ ጩኹ።

36. ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “አሜን፤ እግዚአብሔር ይመስገን” አሉ።

37. ዳዊትም ለእያንዳንዱ ቀን በተመደበው መሠረት ዘወትር እንዲያገለግሉ አሳፍንና የሥራ ባልደረቦቹን በዚያው በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው።

38. እንዲሁም ዖቤድኤዶምና ሥልሳ ስምንቱ የሥራ ባልደረቦቹ አብረዋቸው እንዲያገለግሉ በዚያው ተዋቸው። የኤዶታም ልጅ ዖቤድኤዶምና ሖሳ የቅጥሩ በር ጠባቂዎች ሆኑ።

39. ዳዊት ካህኑን ሳዶቅንና የሥራ ባልደረቦቹን ካህናት በገባዖን ከፍተኛ ቦታ ላይ በሚገኘው በእግዚአብሔር ድንኳን ተዋቸው፤

40. የተዋቸውም ለእስራኤል በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት በእግዚእብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ጧትና ማታ በየጊዜው እንዲያቀርቡ ነው።

41. እንዲሁም “ፍቅሩ ለዘላለም ነውና” እያሉ እንዲያቀርቡ ኤማንና ኤዶታም እንዲሁም ተመርጠውና ስማቸው ተመዝግቦ የተመደቡ ሌሎችም አብረዋቸው ነበሩ።

42. ድምፀ መለከቱንና ጸናጽሉን ለማሰማት፣ ደግሞም መንፈሳዊ መዝሙር ሲዘመር ለሚጠቀሙባቸው ሌሎች መሣሪያዎች ኀላፊዎቹ ኤማንና ኤዶታም ነበሩ፤ የኤዶታምም ልጆች በሩን እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።

43. ከዚያም ሕዝቡ ተነሣ፤ እያንዳንዱም ወደየቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተ ሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ ተመለሰ።