ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 3:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ከእነርሱም አንዲቱ እንዲህ አለች፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን እንኖራለን፤ አብራኝ እያለችም እኔ ልጅ ወለድሁ፤

18. እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላም፣ ይህች ሴት ወለደች፤ ያለ ነው እኛ ብቻ ነን፤ ከሁለታችን በቀር በዚያ ቤት ማንም አልነበረም።

19. “የዚህች ሴት ሕፃን ልጅ ስለ ተኛችበት ሌሊት ሞተ።

20. ስለዚህም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፣ እኔ አገልጋይህ ተኝቼ ሳለሁ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደችው፤ ከዚያም የእኔን ልጅ ራሷ ታቅፋ፣ የሞተ ልጇን አምጥታ በዕቅፌ አደረገችው።

21. በማግሥቱ ልጄን ላጠባ ስነሣ እነሆ ሞቶአል፤ ነገር ግን በማለዳ ብርሃን ትክ ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድሁት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብሁ።

22. ሌላዪቱም ሴት፣ “ነገሩ አንቺ እንደ ምትዪው አይደለም፤ የሞተው የአንቺ፣ በሕይወት ያለውም የእኔ ነው” አለች።የመጀመሪያዋ ሴት ግን አጠንክራ፣ “አይደለም! የሞተው የአንቺ፣ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው” አለች፤ በዚህ ሁኔታም በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።

23. ንጉሡም፣ “ይህችኛዪቱ፣ ‘የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው፣ የአንቺ የሞተው ነው’ ትላለች፤ ያችኛዪቱ ደግሞ፣ ‘አይደለም የአንቺ ልጅ ሞቶአል፣ በሕይወት ያለው የእኔ ነው’ ትላለች” አለ።

24. ከዚያም ንጉሡ፣ “እንግዲያውስ ሰይፍ አምጡልኝ” አለ፤ ለንጉሡም ሰይፍ አመጡለት።

25. በዚህ ጊዜ ንጉሡ፣ “በሉ በሕይወት ያለውን ልጅ ከሁለት ክፈሉና ለአንዷ ግማሹን፣ ለሌላዪቱም ግማሹን ስጡ” ብሎ አዘዘ።

26. በሕይወት ያለው ልጅ እናት ለልጇ እጅግ ስለ ራራች ንጉሡን፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እባክህ በሕይወት ያለውን ሕፃን ለእርሷ ስጣት፤ አትግደለው” አለች።ሌላዪቱ ግን፣ “ለእኔም ሆነ ለአንቺ አይሰጥም፤ ሁለት ላይ ይከፈል!” አለች።

27. ከዚህ በኋላ ንጉሡ፣ “በሉ በሕይወት ያለውን ሕፃን ለመጀመሪያዪቱ ሴት ስጧት፤ አትግደሉት፤ እናቱ እርሷ ናት” አለ።

28. እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ የሰጠውን ፍርድ ሲሰሙ ፈሩት፤ ፍትሕ ለመስጠት የአምላክን ጥበብ የታደለ መሆኑን አይተዋልና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 3