ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:42-53 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

42. ኢዮሣፍጥ ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱ ዓዙባ ትባላለች፤ እርሷም የሺልሒ ልጅ ነበረች።

43. በአካሄዱም ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያች ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ፣ ዕጣንም ያጥን ነበር።

44. እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር በሰላም ኖረ።

45. ሌላውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ የፈጸመው፣ ያከናወነውና ያደረገው ጦርነት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን?

46. ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ።

47. በዚያን ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር።

48. ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የንግድ መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር።

49. በዚያን ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን እሺ አላለውም።

50. ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

51. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በሰማርያ ነገሠ፤ እስራኤልንም ሁለት ዓመት ገዛ።

52. እርሱም የአባቱንና የእናቱን፣ እንዲሁም እስራኤልን ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ ሠራ።

53. አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። በዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ እንዲነሣሣ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22