ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:32-48 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. የሠረገላ አዛዦቹ ኢዮሣፍጥን ሲያዩት፣ “ያለ ጥርጥር ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ስለዚህ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ሲጮህ ግን

33. የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን አውቀው መከታተሉን ተዉት።

34. ነገር ግን አንዱ ቀስቱን ሳያልም እንዲሁ ሲያስፈነጥር በጦር ልብሱ መጋጠሚያ ላይ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው፤ ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን፣ “ቈስያለሁና ወደ ኋላ አዙረህ ከጦሩ ሜዳ አውጣኝ” አለው።

35. ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜም ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት ሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቊስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያኑ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ።

36. ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ።

37. ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ።

38. ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ ኵሬ አጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት።

39. ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝሆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን?

40. አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

41. የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ።

42. ኢዮሣፍጥ ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱ ዓዙባ ትባላለች፤ እርሷም የሺልሒ ልጅ ነበረች።

43. በአካሄዱም ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያች ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ፣ ዕጣንም ያጥን ነበር።

44. እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር በሰላም ኖረ።

45. ሌላውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ የፈጸመው፣ ያከናወነውና ያደረገው ጦርነት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን?

46. ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ።

47. በዚያን ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር።

48. ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የንግድ መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22