ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:14-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ።

15. እዚያም እንደ ደረሰ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ እንዝመትባት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዘምተህ ድል አድርጋት” ብሎ መለሰለት።

16. ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

17. ከዚያም ሚክያስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በየተራራው ላይ ተበትነው አየሁ፣ እግዚአብሔርም፣ ‘ይህ ሕዝብ ጌታ የለውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደየቤቱ ይሂድ’ አለ።”

18. የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

19. ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ስማ፤ ‘እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይ ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ፤

20. እግዚአብሔርም፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት፣ አክዓብን ማን ያስተው?” አለ።’“ታዲያ አንዱ ይህን፣ ሌላውምያን አለ፤

21. በመጨረሻም፣ ‘አንድ መንፈስ ወጣ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፣ “እኔ አስተዋለሁ” አለ።’

22. እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።“እርሱም፣ ‘እኔ እወጣለሁ፤ በገዛ ነቢያቱም አፍ ሁሉ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም፣ “በል እንግዲያው ውጣና አስተው፤ ይሳካልሃል” አለው።

23. “ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ በአንተም ላይ መዓቱን እንደሚያመጣብህ ተናገረ።”

24. ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ በየት በኩል ዐልፎ ነው አንተን መጥቶ ያናገረህ?” ሲል ጠየቀው።

25. ሚክያስም፤ “ይህንማ ለመደበቅ ወደ አንዲት እልፍኝ በሄድህ ዕለት ታውቀዋለህ” አለው።

26. ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “በሉ ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤

27. ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ “በደኅና እስክመለስ ድረስ፣ ይህን ሰው በእስር ቤት አቈዩት፤ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በስተቀር ሌላ እንዳትሰጡት” ብሎአል በሉት’ አለ።

28. ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስህ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረማ!” አለ፤ ከዚያም በመቀጠል፣ “በዚህ ያለኸው ሕዝብ ሁሉ ይህን ቃሌን ልብ ብለህ ያዘው፤” አለ።

29. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ወደምትገኘው ሬማት ወጡ።

30. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እንዳልታወቅ እኔ ልብስ ለውጬና ሌላ ሰው መስዬ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ራሱን ደብቆ ወደ ጦርነቱ ገባ።

31. በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ይሁን ትልቅ ከማንም ጋር እንዳትገጥሙ” ሲል አዞአቸው ነበር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22