ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:11-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ የተባለው የክንዓና ልጅ የብረት ቀንዶች አበጅቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ የምትወጋቸው በእነዚህ ነው’ ” አለው።

12. የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና በገለዓድ የምትገኘውን ሬማትን ወግተህ ድል አድርግ” በማለት በአንድ ቃል ትንቢት ይናገሩ ነበር።

13. ከዚያም ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልእክተኛ፣ “እነሆ፤ ሌሎቹ ነቢያት ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ በአንድ ቃል ትንቢት እየተናገሩለት ነውና ያንተም ቃል ከእነርሱ ጋር አንድ እንዲሆን እባክህ መልካም ነገር ተናገር” አለው።

14. ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ።

15. እዚያም እንደ ደረሰ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ እንዝመትባት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዘምተህ ድል አድርጋት” ብሎ መለሰለት።

16. ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

17. ከዚያም ሚክያስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በየተራራው ላይ ተበትነው አየሁ፣ እግዚአብሔርም፣ ‘ይህ ሕዝብ ጌታ የለውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደየቤቱ ይሂድ’ አለ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22