ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም።

2. በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ።

3. የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው።

4. ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት ላይ ለመዝመት አብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው።ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ ያው እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለ።

5. ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።

6. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ልዝመት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።

7. ኢዮሣፍጥ ግን፣ “የምንጠይቀው የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

8. የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ አንዳችም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ።

9. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “በል የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።

10. የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር አጠገብ ባለው አውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው ሳለ፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

11. በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ የተባለው የክንዓና ልጅ የብረት ቀንዶች አበጅቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ የምትወጋቸው በእነዚህ ነው’ ” አለው።

12. የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና በገለዓድ የምትገኘውን ሬማትን ወግተህ ድል አድርግ” በማለት በአንድ ቃል ትንቢት ይናገሩ ነበር።

13. ከዚያም ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልእክተኛ፣ “እነሆ፤ ሌሎቹ ነቢያት ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ በአንድ ቃል ትንቢት እየተናገሩለት ነውና ያንተም ቃል ከእነርሱ ጋር አንድ እንዲሆን እባክህ መልካም ነገር ተናገር” አለው።

14. ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22