ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 21:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ከዚያም ሁለት የሐሰት ምስክሮች መጥተው ከፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ በሕዝቡም ፊት፣ “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል” ብለው መሰከሩበት። ስለዚህ ከከተማዪቱ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

14. ከዚያም ለኤልዛቤል፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል” ብለው ላኩባት።

15. ኤልዛቤልም በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ወዲያው እንደ ሰማች አክዓብን፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል፤ በል ተነሣና ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ውሰደው” አለችው።

16. አክዓብ የናቡቴን ሞት ሲሰማ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ተነሥቶ ወረደ።

17. ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

18. “ተነሣና በሰማርያ ሆኖ የሚገዛውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ሄዶ አሁን እዚያው ይገኛል።

19. እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰውየውን ገደልኸው፤ ደግሞ ርስቱን ልትወስድ? ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!’ ”

20. አክዓብም ኤልያስን፣ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” አለው።ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ነገር ለማድረግ ራስህን ሸጠሃልና አዎን አግኝቼሃለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 21