ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 19:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት።

2. ስለዚህም እርሷ፣ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ስትል ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።

3. ኤልያስም ፈርቶ ስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤

4. በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ።

5. ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው።በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው።

6. ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ እንጎቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ።

7. የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው።

8. ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤

9. በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 19