ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 18:26-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የበኣልን ስም ጠሩ፤ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር።

27. እኩለ ቀንም ላይ ኤልያስ፣ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ አምላክ አይደለም እንዴ! ምናልባት በሐሳብ ተውጦ ወይም ሥራ በዝቶበት፣ አልያም በጒዞ ላይ ይሆናል፤ ተኝቶም ከሆነ ቀስቅሱት” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር።

28. ስለዚህ እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር።

29. እኩለ ቀን ዐለፈ፤ እነርሱም የሠርክ መሥዋዕት እስኪቀርብ ድረስ የሚዘላብድ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።

30. ከዚያም ኤልያስ ሕዝቡን በሙሉ፣ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

31. ከዚያም ኤልያስ፣ “ስምህ እስራኤል ይባላል” ተብሎ የእግዚአብሔር ቃል በመጣለት በያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ፤

32. በድንጋዮቹም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ዐሥራ አምስት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጒድጓድ ቈፈረ፤

33. ዕንጨቱን ረበረበ፤ የወይፈኑንም ሥጋ በየብልቱ ከቈረጠ በኋላ በዕንጨቱ ላይ አኖረው። ከዚያም፣ “ውሃ በአራት ጋን ሞልታችሁ፣ በመሥዋዕቱና በዕንጨቱ ላይ አፍስሱ” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 18