ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 18:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ታዲያ አንተ ሄጄ ለጌታዬ፤ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤ እርሱም ይገድለኛል!”

15. ኤልያስም፣ “በፊቱ የቆምሁት ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔርን፣ ዛሬ በአክዓብ ፊት በርግጥ እገለጣለሁ” አለ።

16. ስለዚህ አብድዩ ሄዶ ይህንኑ ለአክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ።

17. ኤልያስንም ባየው ጊዜ፤ “እስራኤልን የምታውክ አንተ ነህን?” አለው።

18. ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ።

19. አሁንም ሕዝቡ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲገናኘኝ ለመላው እስራኤል ጥሪ አድርግ። ከኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ አምሳውን የበኣል ነቢያት፣ አራት መቶውንም የአሼራ ነቢያት አምጣቸው።”

20. ስለዚህ አክዓብ በመላው እስራኤል ጥሪ አደረገ፣ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።

21. ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ።ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።

22. ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍሁ እኔ ብቻ ነኝ፤ በኣል ግን አራት መቶ አምሳ ነቢያት አሉት።

23. ሁለት ወይፈኖች ስጡን፤ እነርሱም አንዱን መርጠው ይውሰዱ፤ በየብልቱም ቈራርጠው፣ በዕንጨት ላይ ያኑሩት፤ ግን እሳት አያንድዱበት፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፤ በዕንጨትም ላይ አኖረዋለሁ፤ እሳት አላነድበትም።

24. ከዚያ እናንተ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶ በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።”ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “ያልኸው መልካም ነው” አሉ።

25. ኤልያስም ለበኣል ነቢያት፣ “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ፤ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ግን እሳት አታንድዱበት” አላቸው።

26. ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የበኣልን ስም ጠሩ፤ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 18