ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 17:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚህ ጊዜ ከገለዓድ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፣ “የማመልከው ሕያው እግዚአብሔርን፣ በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” አለው።

2. ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ለኤልያስ መጣለት፤

3. “ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው በኮራት ወንዝ ተሸሸግ።

4. ውሃ ከወንዙ ትጠጣለህ፤ ቊራዎችም እዚያው እንዲመግቡህ አዝዣለሁ።”

5. ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘውን ፈጸመ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ወደ ኮራት ወንዝ ሄዶ በዚያ ተቀመጠ።

6. ቊራዎችም ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ውሃም ከወንዙ ይጠጣ ነበር።

7. በምድሪቱ ላይ ዝናብ ባለመጣሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንዙ ደረቀ።

8. ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፤

9. “ተነሥና ሲዶና ውስጥ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሄደህ ተቀመጥ፤ በዚያም አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ።”

10. ስለዚህ ተነሥቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዪቱ በር እንደ ደረሰም፣ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቃቅም አገኛት፤ ጠርቶም፣ “የምጠጣው ውሃ በዕቃ ታመጪልኛለሽን?” ሲል ለመናት።

11. ልታመጣለት ስትሄድ አሁንም ጠራትና፣ “እባክሽን፣ ቊራሽ እንጀራም ይዘሽልኝ ነይ” አላት።

12. እርሷም መልሳ፣ “አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ዕፍኝ ዱቄትና በማሰሮ ካለው ጥቂት ዘይት በቀር ምንም የለኝም። እነሆ፤ ለራሴና ለልጄ ምግብ አዘጋጅቼ በልተን እንድንሞት ጭራሮ ለቃቅሜ ወደ ቤት ልወስድ ነው” አለችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 17