ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 15:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም።

6. አብያም በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።

7. ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።

8. አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

9. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤

10. በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ አያቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

11. አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።

12. የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ።

13. አስጸያፊውን የአሼራ ምስል ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው።

14. አሳ የማምለኪያ ኰረብታዎችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር የተገዛ ነበር።

15. አባቱና እርሱ ለእግዚአብሔር የቀደሱትን ብርና ወርቅ እንዲሁም ዕቃዎችን አምጥቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት አስገባ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 15