ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 15:22-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ አስቀምጦት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ ንጉሡም በዚሁ ምጽጳንና በብንያም ውስጥ ጌባን ሠራ።

23. በአሳ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በሙሉ፣ ያደረገውም ሁሉና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፈው የሚገኙ አይደሉምን? ንጉሥ አሳ በሸመገለ ጊዜ ግን እግሮቹ ታመሙ።

24. አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮሣፍጥም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

25. በይሁዳ ንጉሥ በአሳ ዘመነ መንግሥት በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።

26. እርሱም በአባቱ መንገድ በመሄድ፣ አባቱ የሠራውንና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመሥራት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

27. ናዳብና መላው እስራኤል በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከበው ሳሉ፣ ከይሳኮር ነገድ የተወለደው የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐምፆ በመነሣት ናዳብን በገባቶን ገደለው።

28. ባኦስ ናዳብን የገደለውና በእግሩ ተተክቶ የነገሠው፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው።

29. ወዲያውኑ እንደ ነገሠም የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ። እግዚአብሔር በሴሎናዊው ባሪያው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረው፣ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀር፣ ሁሉንም አጠፋቸው፤

30. ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ በማነሣሣቱ ነው።

31. ሌላው በናዳብ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ እርሱም ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

32. አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

33. የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በቴርሳ ከተማ፣ በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ሃያ አራት ዓመትም ገዛ።

34. በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 15