ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 13:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው።

18. ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር።

19. ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው አብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም።

20. በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤

21. ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዛት አልጠበቅህም፤

22. ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።

23. የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት።

24. ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር።

25. በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ።

26. ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን ሲሰማ፣ “ይህ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለለው ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ቃል መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ።

27. ከዚያም ነቢዩ ልጆቹን፣ “በሉ አህያ ጫኑልኝ” አላቸውና ጫኑለት።

28. ከዚያም ሄዶ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ አንበሳውና አህያው በአጠገቡ ቆመው አገኘ፤ አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም አልሰበረውም።

29. ስለዚህ፣ ነቢዩ የዚያን የእግዚአብሔር ሰው ሬሳ አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነ፤ አልቅሶ ለመቅበርም ራሱ ወደሚኖርበት ከተማ አመጣው።

30. ከዚያም ሬሳውን በራሱ መቃብር ቀበረው፤ “አወይ ወንድሜን” እያሉም አለቀሱለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 13