ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 13:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. እየጋለበ ያን የእግዚአብሔር ሰው ተከተለው። ከዚያም በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘውና፣ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።

15. ስለዚህ ነቢዩ፣ “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው።

16. የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህ ቦታም አብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤

17. ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው።

18. ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር።

19. ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው አብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም።

20. በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤

21. ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዛት አልጠበቅህም፤

22. ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።

23. የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት።

24. ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር።

25. በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 13