ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 13:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ቃል ታዞ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ።

2. መሠዊያውንም በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነዳል።’ ”

3. በዚያች ዕለት ያ የእግዚአብሔር ሰው፣ እንዲህ ሲል ምልክት ሰጠ፤ “እግዚአብሔር የሰጠውም ምልክት፣ ‘እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው ዐመድ ይፈሳል’ ” የሚል ነው።

4. ንጉሥ ኢዮርብዓምም ያ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል መሠዊያ ላይ ጮኾ የተናገረውን ሲሰማ፣ እጁን መሠዊያው ካለበት በመዘርጋት፣ “ያዙት!” አለ፤ ነገር ግን ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም

5. እንዲሁም ያ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ተመርቶ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ።

6. ከዚያም ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ለምንልኝ፤ ጸልይልኝም” አለው፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡ እጅ ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞዋም ሆነች።

7. ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው።

8. የእግዚአብሔር ሰው ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም።

9. በእግዚአብሔር ቃል፤ ‘እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ ታዝዣለሁና።”

10. ስለዚህም በመጣበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴል ተመለሰ።

11. በዚያን ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም መጥተው በዚያች ዕለት የእግዚአብሔር ሰው እዚያ ያደረገውን ሁሉና ንጉሡንም ምን እንዳለው ለአባታቸው ነገሩት።

12. አባታቸውም፣ “ለመሆኑ የተመለሰው በየትኛው መንገድ ነው?” በማለት ጠየቃቸው፤ ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የተመለሰበትን መንገድ ለአባታቸው አሳዩት።

13. ስለዚህም ልጆቹን፣ “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነርሱም አህያውን ጫኑለትና ተቀምጦበት

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 13