ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 12:14-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ወጣቶቹ የሰጡትን ምክርም ተቀብሎ፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደባችሁ፤ እኔ ደግሞ ከዚያ ይብስ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገረፋችሁ፣ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው።

15. እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም የተናገረው ቀድሞውኑ እግዚአብሔር የወሰነው ስለ ሆነ፣ መፈጸም ነበረበትና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።

16. እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ ለንጉሡ እንዲህ በማለት መለሱ፤“ከዳዊት ምን ድርሻ አለን?ከእሴይስ ልጅ ምን የምናገኘው አለ?እስራኤል ሆይ፤ ወደየድንኳንህ ተመለስ፤ዳዊት ሆይ፤ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!ስለዚህም እስራኤላውያን ወደ ድንኳኖቻቸው ተመለሱ።

17. ሮብዓምም በይሁዳ ምድር በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ገዥ ሆነ።

18. ንጉሥ ሮብዓም የጒልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤል ሁሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።

19. ስለዚህ ሕዝቡ በዳዊት ቤት ላይ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳመፀ ነው።

20. ኢዮርብዓም መመለሱን እስራኤላውያን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ ወደ ጉባኤያቸው በማስጠራት በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት። ለዳዊት ቤት በታማኝነት ጸንቶ የተገኘው የይሁዳ ቤት ብቻ ነው።

21. ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልን ቤት ወግተው መንግሥቱን ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲመልሱ መላውን የይሁዳ ቤትና የብንያምን ነገድ ሰበሰበ፤ የሰራዊቱም ቊጥር አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ነበር።

22. ነገር ግን ይህ የአምላክ ቃል፣ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ሆነው ወደ ሳማያ መጣ፤

23. “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፣ ለመላው የይሁዳ ቤትና ለብንያም ነገድ፣ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ በል፤

24. ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ይህ ነገር ከእኔ የሆነ ነውና ወንድሞቻችሁን እስራኤላውያንን ለመውጋት አትውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ወደየቤታችሁ ተመለሱ።’ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ፤ ወደየቤታቸውም ተመለሱ።

25. ከዚያም ኢዮርብዓም በኰረብታው አገር በኤፍሬም የምትገኘውን ሴኬምን ምሽግ አድርጎ ሠራ፤ በዚያም ተቀመጠ። ደግሞም ያንን ትቶ በመውጣት የጵኒኤልንተ ምሽግ ሠራ።

26. ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ “መንግሥቱ ለዳዊት ቤት የሚመለስ ይመስላል፤

27. ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፣ እንደ ገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።”

28. ንጉሡ ከመከረበት በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጆች አሠርቶ ሕዝቡን፣ “እስራኤል ሆይ፤ ወደ ኢየሩሳሌም እስካሁን የወጣኸው ይበቃል፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው” አለ።

29. አንዱን በቤቴል ሌላውንም በዳን አቆመው።

30. ይህም አድራጎት ኀጢአት ሆነ፤ ሕዝቡም በዚያ ላለው ለመስገድ እስከ ዳን ድረስ ርቆ ሄደ።

31. ኢዮርብዓም በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ አብያተ ጣዖታትን ሠራ፤ ከሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ፣ ሌዋውያን ካልሆኑት ካህናትን ሾመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 12