ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 11:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።

5. ሰሎሞንም የሲዶናውያንን ሴት አምላክ አስታሮትን፣ አስጸያፊውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ።

6. ስለዚህ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም እግዚአብሔርን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።

7. ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው ተራራ ላይ ለአስጸያፊው የሞዓብ አምላክ ለካሞሽ እንዲሁም አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን አምላክ ለሞሎክ ማምለኪያ ኰረብታ ሠራ።

8. ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑና መሥዋዕት ለሚያቀርቡ ለሌሎቹ ሚስቶቹም ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሠራላቸው።

9. ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡ ስለሸፈተ፣ እግዚአብሔር ተቈጣው።

10. ምንም እንኳ ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል ሰሎሞንን ቢከለክለውም፣ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤

11. ስለዚህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ይህን በማድረግህ ያዘዝሁህን ኪዳኔንና ሥርዐቴንም ባለመጠበቅህ፣ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ፤

12. ይህን ግን ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በዘመንህ አላደርገውም፤ መንግሥትህን የምቀዳት ከልጅህ እጅ ነው።

13. ይህም ሆኖ መንግሥቱን በሙሉ አልነጥቀውም፤ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”

14. እግዚአብሔር ከኤዶም ንጉሣዊ ቤተ ሰብ ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰሎሞን ላይ አስነሣው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 11