ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 11:28-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር፤ ሰሎሞንም ወጣቱ ሥራውን እንዴት በሚገባ እንደሚያከናውን ባየ ጊዜ፣ በዮሴፍ ነገድ ለሚሠራው የጒልበት ሥራ ሁሉ ኀላፊ አደረገው።

29. በዚያ ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ሲወጣ፣ የሴሎው ነቢይ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ መጐናጸፊያ ለብሶ ነበር፤ ሁለቱ ብቻቸውን ሳሉ፣

30. አኪያ የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ ይዞ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቀደደው።

31. ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቊራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ መንግሥቱን ከሰሎሞን እጅ እቀዳለሁ፤ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጣለሁ፤

32. ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንድ ነገድ ይቀርለታል፤

33. ይህን የማደርገውም እኔን ትተው የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፣ የሞዓብን አምላክ ካሞሽን፣ የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ስላመለኩ እንዲሁም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ስላልሄዱ በፊቴ ትክክለኛውን ነገር ስላላደረጉ፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ስላልጠበቁ ነው።

34. “ ‘ይሁን እንጂ መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድበትም፤ ስለ መረጥሁት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲገዛ አድርጌዋለሁ።

35. መንግሥትን ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ።

36. ስሜ እንዲኖርባት በመረጥኋት በዚያች በኢየሩሳሌም ከተማ ለባሪያዬ ለዳዊት ምንጊዜም በፊቴ መብራት እንዲኖረው፣ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጣለሁ።

37. አንተን ግን እኔ እወስድሃለሁ፤ ልብህ በወደደው ሁሉ ላይ ትነግሣለህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ትሆናለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 11