ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 10:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።

23. ንጉሥ ሰሎሞንም በሀብትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።

24. ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር።

25. በየዓመቱም የሚመጣውን ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ሽቶ፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።

26. ሰሎሞን ሠረገሎችና ፈረሶች ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት። እነዚህንም ሁሉ ሠረገሎች በሚያኖርበት ከተሞችና ራሱ በሚኖርበት በኢየሩሳሌም እንዲሆኑ አደረገ።

27. ንጉሡም ብሩን በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገ፤ የዝግባውም ዕንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።

28. የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብፅና ከቀዌ ሲሆን፣ እነዚህንም ከቀዌ ገዝተው ያመጧቸው የቤተ መንግሥቱ ንግድ ሰዎች ነበሩ።

29. አንዱን ሠረገላ ከግብፅ የሚያመጡት በስድስት መቶ ሰቅል ብር ሲሆን፣ ፈረሱን ደግሞ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ያመጡ ነበር፤ ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታትም አምጥተው ይሸጡላቸው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 10