ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 1:26-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ነገር ግን እኔን አገልጋይህን፣ ካህኑን ሳዶቅን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስንና አገልጋይህን ሰሎሞንን አልጠራም፤

27. ታዲያ ከእርሱ ቀጥሎ በንጉሥ ጌታዬ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አገልጋዮቹን ሳያሳውቅ ይህ እንዲሆን ንጉሡ ፈቅዶአልን?”

28. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት፣ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” አለ፤ እርሷም ንጉሡ ወዳለበት ገብታ በፊቱ ቆመች።

29. ከዚያም ንጉሡ እንዲህ ሲል ማለ፤ “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳናት ሕያው እግዚአብሔርን!

30. ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በእኔም ምትክ በዙፋኔ ይቀመጣል’ ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር የማልሁልሽን ዛሬ በእውነት እፈጽማለሁ።”

31. ቤርሳቤህም ለጥ ብላ እጅ ከነሣች በኋላ፣ በንጉሡ ፊት ተንበርክካ፣ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ይኑር!” አለች።

32. ንጉሥ ዳዊትም፣ “ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። እነርሱም ንጉሡ ፊት በቀረቡ ጊዜ፣

33. እንዲህ አላቸው፤ “የጌታችሁን አገልጋዮች ይዛችሁ በመሄድ ልጄን ሰሎሞንን በራሴ በቅሎ ላይ አስቀምጡት፤ ወደ ግዮንም ይዛችሁት ውረዱ።

34. በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡት፤ ቀንደ መለከት ነፍታችሁም፣ ‘ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!’ ብላችሁ ጩኹ።

35. አጅባችሁት ወደ ላይ ውጡ፤ ከዚያም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፤ በእኔም ምትክ ይግዛ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ሾሜዋለሁ።”

36. የዮዳሄ ልጅ በናያስም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አሜን! የጌታዬ የንጉሡ አምላክ እግዚአብሔር ይህንኑ ያጽናው።

37. እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር እንደ ነበረ ሁሉ፣ ከሰሎሞንም ጋር ይሁን፤ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው።”

38. ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ወርደው ሰሎሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ አስቀምጠው በማጀብ ወደ ግዮን አመጡት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 1