ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 30:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ሴቶቹን፣ በዚያ የነበሩትን ወጣቶችና ሽማግሌዎቹን ሁሉ ማርከው ወሰዱ፤ የማረኩትንም ይዘው ከመሄድ በስተቀር አንዱንም አልገደሉም ነበር።

3. ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ እንደ ደረሱም፣ እነሆ፤ ከተማዪቱ በእሳት ጋይታ፣ ሚስቶቻቸው፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ተማርከው አገኙ።

4. በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ማልቀስ እስከሚያቅታቸው ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤

5. ሁለቱ የዳዊት ሚስቶች ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያም ተማርከው ነበር።

6. ሰዎቹ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ነፍሳቸው ተመራ ሊወግሩት ስለ ተመካከሩ ዳዊት በጣም ተጨነቀ፤ ነገር ግን ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር በረታ።

7. ከዚያም ዳዊት የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፣ “ኤፉዱን አምጣልኝ” አለው፤ አብያታርም አመጣለት፤

8. ዳዊትም፣ “ይህን ወራሪ ሰራዊት ልከተለውን?’ እደርስባቸዋለሁን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “በእርግጥ ትደርስባቸዋለህ፤ ምርኮውንም ትመልሳለህ፤ ተከተል” ሲል መለሰለት።

9. ስለዚህ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ወደ ቦሦር ወንዝ መጡ፤ ጥቂቶቹም በቦሦር ወንዝ ቈዩ፤

10. ሁለት መቶዎቹ እጅግ ዝለው ስለ ነበር ወንዙን መሻገር አልቻሉምና። ነገር ግን ዳዊትና አራት መቶ ሰዎች መከታተላቸውን ቀጠሉ።

11. እነርሱም በምድረ በዳ አንድ ግብፃዊ አገኙ፤ ወደ ዳዊትም አመጡት፤ የሚጠጣውን ውሃና የሚበላውን ምግብ ሰጡት።

12. እንደዚሁም የበለስ ጥፍጥፍ ቍራሽና ሁለት ደረቅ የወይን ዘለላዎች ሰጡት። ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም እህል ስላልበላ፣ ውሃም ስላልጠጣ ይህን ከበላ በኋላ ነፍሱ ተመለሰች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 30