ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 30:17-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ዳዊት፣ ከዚያች ዕለት ማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፣ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም።

18. ዳዊት አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፣ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ።

19. ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፣ ምርኮም ሆነ ሌላ፣ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም፤ ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ።

20. እንዲሁም ዳዊት የበጉን፣ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” እያሉ መንጋውን ከሌሎች ከብቶች ፊት ለፊት ይነዱ ነበር።

21. ከዚያም ዳዊት፣ እጅግ በመድከማቸው ምክንያት ሊከተሉት ወዳልቻሉት በቦሦር ወንዝ ቀርተው ወደ ነበሩት ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እነርሱ እንደ ቀረቡም ዳዊት ሰላምታ ሰጣቸው።

22. ከዳዊት ተከታዮች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ ግን፣ “አብረውን ስላልዘመቱ ካመጣነው ምርኮ አናካፍላቸውም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ መሄድ ይችላል” አሉ።

23. ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞቼ ሆይ፤ የጠበቀን፣ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በሰጠን ነገር ይህን ማድረግ አይገባችሁም።

24. የምትሉትን ማን ይቀበላችኋል? ከጓዝ ጋር የቀረው ሰው ድርሻ ለጦርነት ከወጣው ሰው ድርሻ ጋር አይበላለጥም፤ ሁሉም እኩል ይካፈላሉ።”

25. ዳዊትም ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ደንብና ሥርዐት አደረገው።

26. ዳዊት ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ፣ ወዳጆቹ ለሆኑት ለይሁዳ ሽማግሌዎች፣ “ከእግዚአብሔር ጠላቶች የተገኘ ስጦታ እነሆ፤” በማለት ከምርኮው ላይ ከፍሎ ላከላቸው።

27. ይህንም፣ በቤቴል፣ በደቡብ ራሞትና በየቲር ለነበሩ፣

28. በኦሮዔር፣ በሢፍሞት፣ በኤሽትሞዓና

29. በራካል እንዲሁም በይረሕምኤላውያንና በቄናውያን ከተሞች ለሚኖሩ፣

30. በሔርማ፣ በቦራሣን፣ በዓታክ፣

31. በኬብሮን እንዲሁም ዳዊትና ሰዎቹ በተዘዋወሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ለነበሩት ላከላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 30