ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 30:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እንደዚሁም የበለስ ጥፍጥፍ ቍራሽና ሁለት ደረቅ የወይን ዘለላዎች ሰጡት። ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም እህል ስላልበላ፣ ውሃም ስላልጠጣ ይህን ከበላ በኋላ ነፍሱ ተመለሰች።

13. ዳዊትም፣ “አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔ ግብፃዊ ስሆን፣ የአንድ አማሌቃዊ ባሪያ ነኝ፤ ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ በነበረበት ጊዜ ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።

14. የከሊታውያንን ደቡብ፣ የይሁዳን ግዛትና የካሌብን ደቡብ ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።”

15. ዳዊትም፣ “ታዲያ ወራሪው ሰራዊት ወዳለበት መርተህ ታደርሰኛለህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “እንደማትገድለኝ ወይም ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ እነዚህ ወራሪዎች ወዳሉበት አደርስሃለሁ” አለው።

16. ዳዊትን ወደ ታች መርቶ ባደረሰው ጊዜም፣ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሣ በየቦታው ተበታትነው ይበሉ፣ ይጠጡና ይዘፍኑ፣ ይጨፍሩም ነበር።

17. ዳዊት፣ ከዚያች ዕለት ማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፣ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም።

18. ዳዊት አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፣ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ።

19. ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፣ ምርኮም ሆነ ሌላ፣ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም፤ ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ።

20. እንዲሁም ዳዊት የበጉን፣ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” እያሉ መንጋውን ከሌሎች ከብቶች ፊት ለፊት ይነዱ ነበር።

21. ከዚያም ዳዊት፣ እጅግ በመድከማቸው ምክንያት ሊከተሉት ወዳልቻሉት በቦሦር ወንዝ ቀርተው ወደ ነበሩት ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እነርሱ እንደ ቀረቡም ዳዊት ሰላምታ ሰጣቸው።

22. ከዳዊት ተከታዮች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ ግን፣ “አብረውን ስላልዘመቱ ካመጣነው ምርኮ አናካፍላቸውም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ መሄድ ይችላል” አሉ።

23. ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞቼ ሆይ፤ የጠበቀን፣ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በሰጠን ነገር ይህን ማድረግ አይገባችሁም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 30