ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 24:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በጥንት አባባል፣ ‘ከክፉ አድራጊዎች ክፉ ድርጊት ይወጣል’ እንደ ተባለ፤ አሁንም እጄ በአንተ ላይ አትሆንም።

14. “የእስራኤል ንጉሥ የወጣው በማን ላይ ነው? አንተስ የምታሳድደው ማንን ነው? የሞተ ውሻን? ወይስ ቁንጫ?

15. አሁንም እግዚአብሔር ዳኛ ሆኖ በመካከላችን ይፍረድ፤ ጒዳዬን ተመልክቶ እርሱው ይሟገትልኝ፤ እኔንም ከእጅህ ነጻ በማውጣት እውነተኛ መሆኔን ይግለጠው።”

16. ዳዊት ይህን ተናግሮ ሲያበቃ ሳኦል፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ የአንተ ድምፅ ነውን?” ሲል ጠየቀው፤ ጮኾም አለቀሰ።

17. እንዲህም አለ፤ “ክፉ ሳደርግብህ፣ በጎ መልሰህልኛልና፣ አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ።

18. ያደረግህልኝን በጎ ነገር ይኸው ነግረኸኛል፤ እግዚአብሔር እኔን በእጅህ ጥሎኝ ነበር፤ አንተ ግን አልገደልኸኝም።

19. ለመሆኑ ጠላቱን አግኝቶ ጉዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ማን ነው? ዛሬ ስላደረግህልኝ ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ።

20. እነሆ፤ አንተ በእርግጥ እንደምትነግሥና የእስራኤል መንግሥት በእጅህ እንደምትጸና ዐውቃለሁ።

21. ዘሮቼን እንዳታጠፋ ስሜንም ከአባቴ ቤት እንዳት ደመስስ አሁን በእግዚአብሔር ማልልኝ።”

22. ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ተመለሰ። ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ ዐምባው ወጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 24