ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 23:18-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ። ከዚያም ዮናታን ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊት ግን እዚያው ሖሬሽ ተቀመጠ።

19. የዚፍ ሰዎች ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል ወጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ ዳዊት ከየሴሞን በስተ ደቡብ በኤኬላ ኰረብታ ላይ በሖሬሽ ምሽጎች ውስጥ በመካከላችን ተደብቆ የለምን?

20. አሁንም ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ደስ ባለህ ጊዜ ና እንጂ፣ እርሱን ለንጉሡ አሳልፎ ለመስጠት እኛ አለን።”

21. ሳኦል እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለእኔ ስለ ተቈረቈራችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤

22. አሁንም ሂዱና አጣሩ ዘወትር የት እንደሆነና በዚያ ያየውን ሰው ለይታችሁ ዕወቁ፤ እጅግ ተንኰለኛ መሆኑን ሰምቻለሁና።

23. የሚደበቅባቸውን ቦታዎች ሁሉ ካያችሁ በኋላ ግልጽ መረጃ ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አብሬችሁ እሄዳለሁ፤ ብቻ በዚያ አገር ይገኝ እንጂ በይሁዳ ነገዶች ሁሉ መካከል ከገባበት ጒድጓድ ገብቼ አወጣዋለሁ።”

24. ስለዚህ ሰዎቹ ለመሄድ ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደ ዚፍ ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሴሞን በስተ ደቡብ በዓረባ ውስጥ ባለው በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ።

25. ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትን ሊፈልጉት ሄዱ፤ እርሱም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ ዐለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ። ሳኦልም ይህን እንደ ሰማ፣ ዳዊትን በማሳደድ ወደ ማዖን ምድረ በዳ ዘልቆ ገባ።

26. ሳኦል በተራራው በአንዱ በኩል ሆኖ ሲያሳድድ፣ ዳዊትና ሰዎቹ ደግሞ በተራራው በሌላ በኩል ከሳኦል ለማምለጥ ይጣደፉ ነበር። ሳኦልና ወታደሮቹ ዳዊትንና ሰዎቹን ከበው ለመያዝ ተቃርበው ሳሉ፣

27. አንድ መልእክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወረውታልና ቶሎ ድረስ!” አለው።

28. ከዚያም ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን ትቶ፣ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ሄደ። ከዚህ የተነሣም የዚያን ቦታ ስም “የመለያያ ዐለት” ብለው ጠሩት።

29. ዳዊትም ከዚያ ወደ ላይ ወጥቶ በዐይንጋዲ ምሽጎች ተቀመጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 23