ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 20:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ዳዊት ግን፣ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሎአል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በነፍስህ እምላለሁ በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀርቶአል” ብሎ ማለ።

4. ዮናታንም ዳዊትን፣ “እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው።

5. ስለዚህ ዳዊት እንዲህ አለ፤ ‘እነሆ፤ ነገ የወር መባቻ በዓል ስለ ሆነ፣ ከንጉሡ ጋር ምሳ መብላት ይጠበቅብኛል፤ ነገር ግን እስከ ከነገ ወዲያ ማታ ድረስ ከዱር ልደበቅ፤

6. አባትህ ከፈለገኝ፣ ‘ለቤተ ዘመዶቹ ሁሉ ዓመታዊ መሥዋዕት የሚቀርብ ስለ ሆነ፣ ዳዊት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ቤተ ልሔም ቶሎ ለመሄድ አጥብቆ ፈቃድ ጠየቀኝ’ ብለህ ንገረው።

7. እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፣ አገልጋይህን የሚያሰጋው የለም፤ ከተቈጣ ግን፣ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግ ጣለህ።

8. አንተ ግን፤ ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ፣ ከአገልጋይህ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና። እኔ በደለኛ ከሆንሁ፣ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!”

9. ዮናታንም፣ “ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ነገር እንዳሰበብህ ባውቅ ኖሮ እንዴት ሳልነግርህ እቀራለሁ?” አለው።

10. ዳዊትም፣ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው።

11. ዮናታን፣ “በል ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ።

12. ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ፤ አባቴን ነገ መርምሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ሰዓት እልክብሃለሁ፤ ስለ አንተ ያለው አመለካከት በጎ ከሆነም አሳውቅሃለሁ።

13. ነገር ግን አባቴ ክፉ አስቦብህ፣ ይህን ሳላሳውቅህ ብቀርና በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፤ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋር ይሁን።

14. አንተም እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ እንዳልገደል የእግዚአብሔርን በጎነት አድርግልኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 20