ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 20:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ዳዊት በአርማቴም ካለችው ከነዋት ዘራማ ሸሽቶ ወደ ዮናታን በመሄድ፣ “ምን አድርጌአለሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ? አባትህ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልገውስ በፊቱ ምን ተገኝቶብኝ ነው?” ሲል ጠየቀው።

2. ዮናታንም፣ “ይህስ ከቶ አይሁንብህ፤ አትሞትም! እነሆ፤ አባቴ ትልቅም ይሁን ትንሽ ማናቸውንም ነገር አስቀድሞ ሳይነግረኝ አያደርገውም። ታዲያ አባቴ ይህን ለምን ይደብቀኛል? ነገሩ እንዲህ አይደለም” ብሎ መለሰለት።

3. ዳዊት ግን፣ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሎአል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በነፍስህ እምላለሁ በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀርቶአል” ብሎ ማለ።

4. ዮናታንም ዳዊትን፣ “እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው።

5. ስለዚህ ዳዊት እንዲህ አለ፤ ‘እነሆ፤ ነገ የወር መባቻ በዓል ስለ ሆነ፣ ከንጉሡ ጋር ምሳ መብላት ይጠበቅብኛል፤ ነገር ግን እስከ ከነገ ወዲያ ማታ ድረስ ከዱር ልደበቅ፤

6. አባትህ ከፈለገኝ፣ ‘ለቤተ ዘመዶቹ ሁሉ ዓመታዊ መሥዋዕት የሚቀርብ ስለ ሆነ፣ ዳዊት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ቤተ ልሔም ቶሎ ለመሄድ አጥብቆ ፈቃድ ጠየቀኝ’ ብለህ ንገረው።

7. እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፣ አገልጋይህን የሚያሰጋው የለም፤ ከተቈጣ ግን፣ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግ ጣለህ።

8. አንተ ግን፤ ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ፣ ከአገልጋይህ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና። እኔ በደለኛ ከሆንሁ፣ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!”

9. ዮናታንም፣ “ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ነገር እንዳሰበብህ ባውቅ ኖሮ እንዴት ሳልነግርህ እቀራለሁ?” አለው።

10. ዳዊትም፣ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው።

11. ዮናታን፣ “በል ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ።

12. ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ፤ አባቴን ነገ መርምሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ሰዓት እልክብሃለሁ፤ ስለ አንተ ያለው አመለካከት በጎ ከሆነም አሳውቅሃለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 20