ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 2:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. “ይህን ያህል በመታበይ አትናገሩ፤እንዲህ ያለውም የእብሪት ቃል ከአፋችሁ አይውጣ፤ እግዚአብሔር አምላክ ዐዋቂ ነውና፤ሥራም ሁሉ በእርሱ ይመዘናል።

4. “የኀያላን ቀስቶች ተሰባብረዋል፤ደካሞች ግን በኀይል ታጥቀዋል።

5. ጠግበው የነበሩ ለእንጀራ ሲሉ ተገዙ፤ተርበው የነበሩ ግን እንጀራ ጠገቡ፤መካኒቱ ሰባት ልጆች ወልዳለች፤ብዙ ወንዶች ልጆች ወልዳ የነበረችው ግን መከነች።

6. “እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ያወጣልም።

7. እግዚአብሔር ያደኸያል፤ ያበለጽጋልም፤ያዋርዳል፤ ከፍ ከፍም ያደርጋል።

8. እርሱ ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤ምስኪኑንም ከጒድፍ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ከመኳንንቱ ጋር ያስቀምጣቸዋል፤የክብር ዙፋንም ያወርሳቸዋል።“የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፣ዓለምን በእነርሱ ላይ አድርጎአል።

9. እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል፤ክፉዎች ግን በጨለማ ውስጥ ይጣላሉ፤“ሰው በኀይሉ ድል አያደርግም፤

10. ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ፤እርሱ ከሰማይ ያንጐደጒድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል።“ለንጉሡ ኀይልን ይሰጣል፤የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”

11. ከዚያ በኋላ ሕልቃና ወደ ቤቱ ወደ ራማ ሄደ፤ ብላቴናው ግን በካህኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።

12. የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር።

13. በዚያን ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚፈጽሙት ወግ ነበር፤ ይኸውም ማንም ሰው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይመጣል፤

14. ወደ ድስቱ ወይም ወደ ቶፋው ወይም ወደ አፍላሉ፣ ወይም ወደ ምንቸቱ ይሰደዋል። ከዚያም ካህኑ ሜንጦው ያወጣውን ማናቸውንም ሥጋ ለራሱ ይወስደዋል። ወደ ሴሎ የሚመጡትን እስራኤላውያን ሁሉ የሚያስተናግዱት በዚህ ዐይነት ነበር።

15. ነገር ግን ሥቡ ገና ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መጥቶ መሥዋዕት የሚያቀርበውን ሰው፣ “ካህኑ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ ስለማይቀበል፣ ለካህኑ የሚጠበስ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር።

16. ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ ያለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር።

17. ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 2