ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 2:16-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ ያለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር።

17. ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ።

18. ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር።

19. እናቱም ከባሏ ጋር ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር።

20. ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።

21. እግዚአብሔርም ሐናን ባረካት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

22. በዚህ ጊዜ ዔሊ እጅግ አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በመላው እስራኤል ያደርጉ የነበረውን፣ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሰማ።

23. ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ከመላው ሕዝብ እሰማለሁ፤ ለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?

24. ልጆቼ ሆይ፤ ትክክል አይደላችሁም፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ተሠራጭቶ የምሰማባችሁ ወሬ ጥሩ አይደለም።

25. አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል፣ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ይፈርዳል፤ ነገር ግን ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል፣ ማን ይማልድለታል?” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም።

26. ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ።

27. በዚህ ጊዜ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአባትህ ቤት በግብፅ ምድር በፈርዖን እጅ በነበረ ጊዜ ራሴን ገለጥሁለት?

28. የእኔ ካህን እንዲሆን፣ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፣ ዕጣን እንዲያጥን፣ በፊቴም ኤፉድ እንዲለብስ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ አባትህን መረጥሁት። ደግሞም እስራኤላውያን በእሳት የሚያቀርቡትን ቊርባን ሁሉ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።

29. ታዲያ በማደሪያዬ እንዲቀርብ ያዘዝሁትን መሥዋዕትና ቊርባን የናቃችሁ ለምንድን ነው? አንተና ልጆችህ ሕዝቤ እስራኤል ካቀረበው ቊርባን ሁሉ ምርጥ ምርጡን በልታችሁ ራሳችሁን በማወፈር ከእኔ ይልቅ ልጆችህን የምታከብራቸው ስለምንድን ነው?’

30. “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ቤትህና የአባትህ ቤት በፊቴ ለዘላለም ያገለግሉኝ ዘንድ ተስፋ ሰጥቼ ነበር፤’ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ከእንግዲህ አላደርገውም፤ የሚያከብሩኝን አከብራለሁ፤ የሚንቁኝም ፈጽሞ ይናቃሉ።

31. እነሆ፤ በዘርህ ሽማግሌ እንዳይገኝ ያንተን ኀይልና የአባትህን ቤተ ሰብ ኀይል የምሰብርበት ጊዜ ይመጣል፤

32. በማደሪያዬም መከራ ታያለህ፤ ምንም እንኳ ለእስራኤል በጐ ነገር ቢደረግም፣ በቤተ ሰብህ ውስጥ ሽማግሌ ፈጽሞ አይገኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 2