ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 18:15-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሳኦልም፣ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ፈራው፤

16. መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና።

17. ሳኦል ዳዊትን፣ “ታላቋ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የእግዚአብሔርንም ጦርነቶች ተዋጋ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፣ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበርና።

18. ዳዊት ግን ሳኦልን፣ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤም ሆነ የአባቴ ጐሣስ በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለው።

19. ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች።

20. በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው።

21. ሳኦልም በልቡ፣ “ወጥመድ እንድትሆነው፣ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን፣ “እነሆ፤ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው።

22. ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፣ “ለዳዊት፣ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለ ሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው።

23. እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ አማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቈጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እምብዛም የማልታወቅ ሰው ነኝ” አላቸው።

24. የሳኦል ባለሟሎችም ዳዊት ያላቸውን በነገሩት ጊዜ፣

25. ሳኦል፣ “ዳዊትን፣ ‘ንጉሡስ ለልጅቱ ካንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን ለመበቀል የመቶ ፍልስጥኤማውያንን ሸለፈት እንጂ ሌላ አይደለም ብላችሁ ንገሩት’ ” አላቸው። ሳኦል ይህን ያቀደው ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ነበር።

26. ባለሟሎቹ ይህን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሥ ዐማች መሆኑ ደስ አሰኘው። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት፣

27. ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎቹ ሄደው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ለንጉሡ ዐማች ይሆን ዘንድ፣ ሸለፈታቸውን አምጥቶ በቊጥራቸው ልክ ለንጉሡ አቀረበ፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት።

28. ሳኦል እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደሆነና ልጁ ሜልኮልም እንደ ወደደችው በተረዳ ጊዜ፣

29. ሳኦል ከቀድሞው ይልቅ ፈራው፤ እስከ ዕድሜውም ፍጻሜ ድረስ ጠላቱ ሆነ።

30. የፍልስጥኤማውያን ጦር አዛዦች እንደ ወትሮው ሁሉ፣ ለጦርነት ይወጡ ነበር፤ ዳዊትም ከቀሩት የሳኦል መኳንንት የበለጠ ድል አገኘ፤ ስሙም የታወቀ ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 18