ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 18:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በኀይል መጣበት፣ በዚህ ጊዜ ዳዊት ወትሮ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር፣ ሳኦል በቤቱ ሆኖ ትንቢት ይናገር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤

11. እርሱም፣ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።

12. እግዚአብሔር ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለ ሆነ፣ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።

13. ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺህ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሰራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር።

14. እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር።

15. ሳኦልም፣ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ፈራው፤

16. መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና።

17. ሳኦል ዳዊትን፣ “ታላቋ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የእግዚአብሔርንም ጦርነቶች ተዋጋ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፣ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበርና።

18. ዳዊት ግን ሳኦልን፣ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤም ሆነ የአባቴ ጐሣስ በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለው።

19. ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች።

20. በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው።

21. ሳኦልም በልቡ፣ “ወጥመድ እንድትሆነው፣ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን፣ “እነሆ፤ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው።

22. ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፣ “ለዳዊት፣ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለ ሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው።

23. እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ አማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቈጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እምብዛም የማልታወቅ ሰው ነኝ” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 18