ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 14:35-52 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።

36. ሳኦልም፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስ ቀርላቸው” አለ።እነርሱም፣ “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት።ካህኑ ግን፣ “እዚሁ እግዚአብሔርን እንጠይቅ” አለ።

37. በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያች ቀን አልመለሰለትም።

38. ስለዚህ ሳኦል እንዲህ አለ፤ “የሰራዊቱ መሪዎች ሁላችሁም ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ምን ኀጢአት እንደ ተሠራ እንወቅ።

39. እስራኤልን የታደገ ሕያው እግዚአብሔርን! አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም።

40. ሳኦልም እስራኤላውያንን ሁሉ፣ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው።ሰዎቹም፣ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ብለው መለሱለት።

41. ከዚያ በኋላ ሳኦል፣ “ትክክለኛውን መልስ ስጠኝ” ሲል ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ዕጣው በሳኦልና በዮናታን ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ።

42. ሳኦልም በእኔና በልጄ በዮናታን መካከልም ዕጣ ጣሉ” አላቸው። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወደቀ።

43. ከዚያም ሳኦል ዮናታንን፣ “እስቲ ያደረግኸውን ንገረኝ” አለው።ዮናታንም፣ “በዘንጌ ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ፤ እነሆ፤ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።

44. ሳኦልም፣ “ዮናታን፣ አንተ ካልተገደልህ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፣ የከፋም ነገር ያምጣብኝ” አለ።

45. ሕዝቡ ግን ሳኦልን፣ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? አይደረግም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለ ሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ከራስ ጠጒሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ።

46. ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሰ፤ እነርሱም ወደ አገራቸው ተመለሱ።

47. ሳኦል በእስራኤል ላይ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ፣ በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን ማለትም ሞዓብን፣ አሞናውያንን፣ ኤዶምን፣ የሱባን ነገሥታትና ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው። በሄደበት ሁሉ ድል ይነሣ ነበር።

48. በጀግንነት ተዋግቶ አማሌቃውያንን አሸነፈ፤ እስራኤልንም ይዘርፏቸው ከነበሩት እጅ ታደጋቸው።

49. የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ የሱዊ፣ሜልኪሳ ነበሩ፤ ሴቶች ልጆቹም ትልቋ ሜሮብ፣ ትንሿ ሜልኮል ይባሉ ነበር።

50. የሳኦል ሚስት አኪናሆም የምትባል የአኪማአስ ልጅ ነበረች፤ የሰራዊቱም አዛዥ አበኔር የሚባል የአጎቱ የኔር ልጅ ነበረ።

51. የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር ሁለቱም የአቢኤል ልጆች ነበሩ።

52. በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ነበረ፤ ስለዚህ ሳኦል ብርቱ ወይም ጀግና ሰው ባየ ቊጥር ወደ ራሱ ወስዶ እንዲያገለግለው ያደርግ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 14