ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ፊልጵስዩስ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፣ ወንድሞቼ ደስታዬና አክሊሌ የሆናችሁ፣ እንዲሁም ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ሁኔታ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ።

የጳውሎስ ምክር

2. በጌታ አንድ ልብ እንዲኖራቸው ኤዎድ ያንን እለምናለሁ፤ ሲንጤኪንንም እለምናለሁ።

3. አዎን፤ አንተ ታማኝ የሥራ ባልደረባዬ ሆይ፤ ወንጌልን በማሰራጨት ረገድ ከእኔና ከቀሌምንጦስ ጋር፣ እንዲሁም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎች የሥራ ጓደኞቼ ጋር የተጋደሉትን እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ።

4. ምንጊዜም በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ።

5. ገርነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ቅርብ ነው።

6. በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ።

7. ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።

8. በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።

9. ከእኔ የተማራችሁትን ወይም የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን ወይም ያያችሁትን ማናቸውንም ነገር አድርጉ፤ የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

ላደረጉት ችሮታ የቀረበ ምስጋና

10. ከብዙ ጊዜ በኋላ በአዲስ መንፈስ ስለ እኔ ማሰብ በመጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በርግጥ በተግባር ለመግለጽ ዕድሉ አልነበራችሁም እንጂ ማሰቡንስ ታስቡልኝ ነበር።

11. ይህን የምለው ስለቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣

12. ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብም፣ ባገኝም ሆነ ባጣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።

13. ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ።

14. ሆኖም የመከራዬ ተካፋይ ስለ ሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል።

15. ከዚህም በላይ፣ እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ በመጀመሪያ ወንጌልን በተቀበላችሁ ጊዜ ከመቄዶንያ ስነሣ፣ ከእናንተ በቀር በመስጠትና በመቀበል የትኛውም ቤተ ክርስቲያን አልተባበረም።

16. በተሰሎንቄ በነበርሁበት ጊዜ እንኳ፣ በችግሬ ወቅት ደጋግማችሁ ርዳታ ልካችሁልኛልና።

17. ይኸውም ትርፉ ለእናንተ እየበዛ እንዲሄድ እንጂ ስጦታውን ጓጒቼ አይደለም።

18. የሚያስፈልገኝን ሁሉ፣ ከሚያስፈልገኝም በላይ ተቀብያለሁ፤ የላካችሁትንም ስጦታ ከአፍሮዲጡ እጅ ተቀብዬ ተሞልቻለሁ፤ ይህም መዐዛው የጣፈጠ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው።

19. አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል።

20. ለአምላካችንና ለአባታችን ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

የስንብት ሰላምታ

21. ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእኔ ጋር ያሉት ወንድሞችም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

22. ቅዱሳንን ሁሉ፣ በተለይም ከቄሳር ቤተ ሰው የሆኑት ወገኖች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

23. የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።