ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ፊልጵስዩስ 2:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤

7. ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ራሱን ባዶ አደረገ፤

8. ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ራሱን ዝቅ አደረገ፤እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከመሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።

9. ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤

10. ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣

11. ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

12. ስለዚህ፣ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤

13. እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።

14. ማንኛውንም ነገር ሳታጒረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤

15. ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው።

16. የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።

17. ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስ እንኳ ከሁላችሁ ጋር ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ።

18. እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋር ደስ ልትሰኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል።

19. ስለ እናንተ ሰምቼ ደስ እንዲለኝ፣ ጢሞቴዎስን ቶሎ ወደ እናንተ ልልክላችሁ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ።

20. ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገደው እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም፤

21. ሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯ ጣሉና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ፊልጵስዩስ 2