ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ፊልጵስዩስ 1:9-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ፍቅራችሁ በጥልቅ እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ።

10. ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣

11. ለእግዚእብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው።

12. አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ መርዳቱን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።

13. ከዚህ የተነሣ እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቆአል።

14. በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል።

15. አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ።

16. እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤

17. እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ አስበው በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ።

18. ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል።አዎን፤ ደስ ይለኛል፤

19. በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና።

20. በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል።

21. ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ፊልጵስዩስ 1