ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ፊልጵስዩስ 1:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል።አዎን፤ ደስ ይለኛል፤

19. በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና።

20. በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል።

21. ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው።

22. በሥጋ ከቈየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም።

23. በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋር ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና።

24. ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ለእናንተ ይበልጥ አስፈላጊ ነው።

25. ይህን በማስተዋል፣ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ፣ በሁላችሁ ዘንድ እንደምቈይና እንደምኖር ተረድቻለሁ።

26. እንደ ገና መጥቼ በእናንተ ዘንድ በምሆንበት ጊዜ በእኔ ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁ ደስታ ይበዛላችኋል።

27. ብቻ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤ ይህ ከሆነ መጥቼ ባያችሁ ወይም በርቀት ሆኜ ስለ እናንተ ብሰማ፣ ለወንጌል እምነት እንደ አንድ ሰው ሆናችሁ በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ እንደምትቆሙ ዐውቃለሁ።

28. በማንኛውም መንገድ በተቃዋሚዎቻችሁ አትሸበሩ፤ ይህ እነርሱ እንደሚጠፉ፣ እናንተ ግን እንደምትድኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምልክት ነው።

29. በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቶአችኋልና፤

30. ቀድሞ እንዳያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ፊልጵስዩስ 1