ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 6:3-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል።

4. እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል፤

5. እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋልና።

6. ማንም ቃሉን የሚማር፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ከመምህሩ ጋር ይካፈል።

7. አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል።

8. ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።

9. በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤ ተስፋ ካልቈረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን።

10. ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ።

11. እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ ተመልከቱ።

12. ውጫዊ በሆነ ነገር ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ትገረዙ ዘንድ ሊያስገድዷችሁ ይጥራሉ፤ ይህንም የሚያደርጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ነው።

13. እነርሱ በሥጋችሁ ለመመካት ሲሉ እንድትገረዙ ፈለጉ እንጂ፣ የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን የሚጠብቁ አይደሉም።

14. ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር፣ ሌላው ትምክሕት ከእኔ የራቀ ይሁን።

15. መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።

16. ይህን ትእዛዝ በሚከተሉ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በሆነው እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።

17. እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።

18. ወንድሞች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 6