ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 4:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከዓለም መሠረታዊ ትምህርት ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር።

4. ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤

5. ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው።

6. ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።

7. ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።

8. እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤

9. አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በእርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን?

10. ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ።

11. ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።

12. ወንድሞች ሆይ፤ እለምናችኋለሁ፤ እኔ እናንተን እንደ መሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ። እናንተ አንዳች አልበደላችሁኝም።

13. እንደምታውቁት በመጀመሪያ ለእናንተ ወንጌልን የሰበክሁት፣ በሕመም ምክንያት ነበር።

14. ሕመሜ ለእናንተ ፈተና ሆኖባችሁም እንኳ፣ አልሰለቻችሁኝም፤ ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንዲያውም እንደ ራሱ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 4