ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 4:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ስለ እናንተ ግራ በመጋባት ተጨንቄአለሁና፤ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ ቋንቋ ልናገራችሁ ምን ያህል በወደድሁ!

21. እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን?

22. አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፎአልና።

23. ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ፣ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነው።

24. እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት።

25. እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል፣ አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና።

26. ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት።

27. እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤ደስ ይበልሽ፤አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣በእልልታ ጩኺ፤ባል ካላት ይልቅ፣የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”

28. እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ።

29. በዚያን ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው፣ ልጅ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው።

30. ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከልጇ ጋር አስወግዳት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋር አይወርስምና” ይላል።

31. ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 4