ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 4:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሕመሜ ለእናንተ ፈተና ሆኖባችሁም እንኳ፣ አልሰለቻችሁኝም፤ ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንዲያውም እንደ ራሱ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ።

15. ለመሆኑ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ደረሰ? ቢቻላችሁ ዐይናችሁን ቢሆን እንኳ አውጥታችሁ የምትሰጡኝ እንደ ነበራችሁ እመሰክራለሁ።

16. እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?

17. እነዚያ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሊወስዷችሁ ይተጋሉ፤ ለበጎ ግን አይደለም፤ የሚፈልጉት እናንተን ከእኛ ነጥለው የራሳቸው ሊያደርጓችሁ ነው።

18. ለበጎ እስከ ሆነ ድረስ ተቈርቋሪ መሆን መልካም ነው፤ ይህም መሆን የሚገባው ዘወትር እንጂ እኔ ከእናንተ ጋር ሳለሁ ብቻ አይደለም።

19. የምወዳችሁ ልጆቼ ሆይ፤ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ ስለ እናንተ እንደ ገና ምጥ ይዞኛል፤

20. ስለ እናንተ ግራ በመጋባት ተጨንቄአለሁና፤ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ ቋንቋ ልናገራችሁ ምን ያህል በወደድሁ!

21. እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን?

22. አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፎአልና።

23. ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ፣ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነው።

24. እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት።

25. እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል፣ አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና።

26. ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 4