ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 3:18-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል።

19. ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር።

20. ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።

21. ታዲያ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? ከቶ አይደለም፤ ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥም ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር።

22. መጽሐፍ ግን ዓለም ሁሉ የኀጢአት እስረኛ መሆኑን ያውጃል፤ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው ተስፋ ለሚያምኑት ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው።

23. ይህ እምነት ከመምጣቱ በፊት በሕግ አማካይነት እስረኞች ሆነን፣ እምነት እስከሚገለጥ ድረስ ተዘግቶብን ነበርን።

24. ስለዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን ሞግዚታችን ሆነ።

25. አሁን ግን ያ እምነት ስለ መጣ፣ ከእንግዲህ በሕግ ሞግዚትነት ሥር አይደለንም።

26. ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤

27. ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና።

28. በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ።

29. የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 3