ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 3:16-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው።

17. የምለው እንዲህ ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም።

18. ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል።

19. ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር።

20. ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።

21. ታዲያ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? ከቶ አይደለም፤ ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥም ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር።

22. መጽሐፍ ግን ዓለም ሁሉ የኀጢአት እስረኛ መሆኑን ያውጃል፤ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው ተስፋ ለሚያምኑት ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 3