ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 6:42-62 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

42. ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’” አሉ።

43. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤

44. የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

45. በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።

46. ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው።

47. እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።

48. የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።

49. አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ።

50. ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው።

51. ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”

52. አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር።

53. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።

54. ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤

55. ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤

56. ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ።

57. ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል።

58. ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።”

59. ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኲራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።

60. ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ።

61. ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጒረም ረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን?

62. ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 6