ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 6:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ተቃርቦ ነበር።

5. ኢየሱስም ቀና ብሎ ሲመለከት ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ፤ ፊልጶስንም፣ “እነዚህ ሰዎች እንዲበሉ እንጀራ ከየት እንግዛ?” አለው።

6. ይህን የጠየቀው ሊፈትነው እንጂ ራሱ ሊያደርግ ያሰበውን ያውቅ ነበር።

7. ፊልጶስም፣ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲቃመስ ለማድረግ፣ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ እንኳ አይበቃም” ሲል መለሰ።

8. ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስም፣ እንዲህ አለ፤

9. “አምስት ትንንሽ የገብስ እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይዳረሳል?”

10. ኢየሱስም፣ “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በዚያ ቦታ ብዙ ሣር ነበረ፤ አምስት ሺህ ያህል ወንዶችም ተቀመጡ።

11. ኢየሱስ አምስቱን እንጀራ አንሥቶ አመሰገነ፤ ለተቀመጡትም የሚፈልጉትን ያህል ዐደለ፤ ዓሣውንም እንዲሁ።

12. ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከተረፈው ቊርስራሽ ምንም እንዳ ይባክን ሰብስቡ” አላቸው።

13. እነርሱም፣ ከተበላው አምስት የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቊርስራሽ ሰብስበው ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።

14. ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ፣ “ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ በርግጥ ይህ ነው” አሉ።

15. ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ።

16. በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፤

17. በጀልባውም ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም ለመሻገር ተነሡ። ጊዜው መሽቶ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ እነርሱ ገና አልመጣም ነበር።

18. ኀይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለ ነበር ባሕሩ ተናወጠ።

19. አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል እንደ ቀዘፉ፣ ኢየሱስ በውሃ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲመጣ አይተው ደነገጡ።

20. እርሱ ግን፣ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።

21. እነርሱም እንዲሳፈር ፈለጉ፤ ጀልባዋም ወዲያውኑ ወደሚሄዱበት ዳርቻ ደረሰች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 6