ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 6:20-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. እርሱ ግን፣ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።

21. እነርሱም እንዲሳፈር ፈለጉ፤ ጀልባዋም ወዲያውኑ ወደሚሄዱበት ዳርቻ ደረሰች።

22. በማግሥቱ በባሕሩ ማዶ የቀሩት ሰዎች በዚያ አንዲት ጀልባ ብቻ እንደ ነበረች ተረዱ፤ ኢየሱስ እንዳልተሳፈረና ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን እንደሄዱም ዐወቁ።

23. ከዚያም በኋላ፣ ሌሎች ጀልባዎች ከጥብር ያዶስ፣ ሕዝቡ ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በላበት ስፍራ መጡ።

24. ሰዎቹም፣ ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን እንዳወቁ፣ ኢየሱስን ፍለጋ በጀልባዎቹ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ።

25. ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፣ “ረቢ፤ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት።

26. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።

27. ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በእርሱ ላይ አትሞአልና።”

28. እነርሱም፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” አሉት።

29. ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው።

30. ስለዚህ እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ “አይተን እንድናምንህ ምን ታምራዊ ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ?

31. ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራን ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።”

32. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ ግን አባቴ ነው፤

33. የእግዚአብሔር እንጀራ እርሱ ከሰማይ የሚወርድ፣ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።”

34. እነርሱም፣ “ጌታ፣ እንግዲያውስ ይህን እንጀራ ሁል ጊዜ ስጠን” አሉት።

35. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 6