ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 3:6-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው።

7. ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤

8. ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።”

9. ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።

10. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን?

11. እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም።

12. ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?

13. ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም።

14. ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤

15. ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።

16. “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤

17. እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው።

18. በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል።

19. ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤

20. ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም።

21. በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”

22. ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም።

23. በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ፣ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር።

24. ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 3